Esther 2

አስቴር ንግሥት ሆነች

1ከዚህ በኋላ ንጉሡ ጠረክሲስ ቍጣው ሲበርድለት አስጢንን፣ ያደረገችውን ነገርና በእርሷም ላይ ያስተላለፈውን ዐዋጅ ዐሰበ። 2ከዚያም የንጉሡ የቅርብ አገልጋዮች እንዲህ የሚል ሐሳብ አቀረቡ፤ “ለንጉሡ ቈንጆ ልጃገረዶች ይፈለጉለት፤ 3እነዚህን ሁሉ ቈንጆ ልጃገረዶች በሱሳ ግንብ ወደሚገኘው ልዩ የሴቶች መኖሪያ ቦታ እንዲያመጡ፣ ንጉሡ በግዛቱ በሚገኙት አውራጃዎቹ ሁሉ ባለ ሥልጣኖችን ይሹም፤ እነርሱም የሴቶች የበላይ ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሄጌ ኀላፊነት ሥር ይሁኑ፤ የውበትም እንክብካቤ ይደረግላቸው። 4ከዚያም ንጉሡን ደስ የምታሰኘው ልጃገረድ በአስጢን ፈንታ ንግሥት ትሁን።” ምክሩ ንጉሡን ደስ አሰኘው፤ በተባለውም መሠረት አደረገ።

5በዚህ ጊዜ ከብንያም ነገድ የቂስ ልጅ፣ የሰሜኢ ልጅ፣ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ በሱሳ ግንብ ይኖር ነበር፤ 6እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን
በዕብራይስጥ፣ ኢኮንያን የሚለው ስም ኢዮአቄም ከሚለው ጋር አንድ ዐይነት ነው።
ጋር ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት አንዱ ነበር።
7መርዶክዮስ አንዲት ሀደሳ የምትባል የአጎቱ ልጅ ነበረችው፤ አባትና እናት ስላልነበራት፣ ያሳደጋት እርሱ ነበር። አስቴር ተብላ የምትጠራው ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች። አባቷና እናቷ ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት።

8የንጉሡ ትእዛዝና ዐዋጅ በወጣ ጊዜ፣ ብዙ ልጃገረዶች ወደ ሱሳ ግንብ ተወስደው ለጠባቂው ለሄጌ ተሰጡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ተወስዳ፣ ለሴቶቹ ጠባቂ ለሄጌ በዐደራ ተሰጠች። 9ልጃገረዲቱም ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች፤ እርሱም የውበት መንከባከቢያዋንና የተለየ ምግብ ወዲያውኑ ሰጣት። ከቤተ መንግሥቱ የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮችን በመመደብም እርሷንና ደንገጡሮቿን ምርጥ ወደ ሆነው የሴቶች መጠበቂያ አዛወረ።

10መርዶክዮስ እንዳትናገር አዝዟት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደ ሆነች አልገለጸችም። 11መርዶክዮስም አስቴር እንዴት እንደ ሆነችና ምንስ እንዳጋጠማት ለማወቅ፣ በየዕለቱ በሴቶች መጠበቂያ አደባባይ አጠገብ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።

12አንዲት ልጃገረድ ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ዘንድ ለመግባት ተራዋ ከመድረሱ በፊት ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ ልዩ ልዩ ሽቱ በመቀባትና በተለያዩ የፊት ቀለሞች በመዋብ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ወር መቈየት ነበረባት፤ 13ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትገባውም በዚህ ሁኔታ ሲሆን፣ ሴቶቹ ከሚኖሩበት ስፍራ ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ስትሄድ፣ መውሰድ የምትፈልገው ማናቸውም ነገር ይሰጣት ነበር። 14ሲመሽ ወደዚያው ትሄዳለች፤ ሲነጋም የቁባቶች ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሻአሽጋዝ ጥበቃ ሥር ወደሚገኘው ወደ ሌላው የሴቶች መጠበቂያ ቤት ትመለሳለች፤ ደስ የተሰኘባት ካልሆነችና በስሟም ካልጠራት ዳግመኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ አትገባም።

15መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የአጎቱ የአቢካኢል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትሄድበት ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ልዩ ጥበቃ ቤት ኀላፊ የሆነው ሄጌ የነገራትን እንጂ፣ ሌላ ምንም አልጠየቀችም። አስቴር በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች። 16በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት በተባለው በዐሥረኛው ወር ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ተወሰደች።

17በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት። 18ንጉሡም ስለ አስቴር ክብር ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በዓሉም በየአውራጃዎቹ ሁሉ እንዲከበር ዐወጀ፤ በንጉሣዊ ልግስናውም ስጦታ አደረገ።

መርዶክዮስ በንጉሡ ላይ የተጠነሰሰውን ሤራ ደረሰበት

19ደናግሉ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰብስበው ሳለ፣ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር። 20አስቴር ግን ልክ መርዶክዮስ እንደ ነገራት የማን ወገንና የየት አገር ሰው እንደ ሆነች ደብቃ ነበር፤ ይህ የሆነበት ምክንያት መርዶክዮስ በሚያሳድጋት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ፣ አሁንም ምክሩን ትከተል ስለ ነበር ነው።

21መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ፣ በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አለቆች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፤ ንጉሥ ጠረክሲስንም ለመግደል ዶለቱ። 22መርዶክዮስም አድማውን ስለ ደረሰበት፣ ለንግሥት አስቴር ገለጠላት፤ እርሷም ይህን ከመርዶክዮስ ማግኘቷን ለንጉሡ ገልጣ ነገረችው። 23ነገሩ ሲጣራም እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ሁለቱም ሹማምት በስቅላት ሞት ተቀጡ። ይህ ሁሉ በንጉሡ ፊት በታሪክ መዝገብ ተጻፈ።

Copyright information for AmhNASV